ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በቢታንያ አልዓዛር ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም የሚገኘውን የአረጋውያን መጦሪያና ማረፊያ ጎበኙ።
ሪፖርተር ሰላም
ገዳሙ በውስጡ ስድስት ኢትዮጵያውያን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በክብር ያረፉበት መካነ መቃብር የያዘ ቅዱስ ሥፍራ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
(#EOTCTV ነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ኢየሩሳሌም )
ነሐሴ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገዳማት መካከል አንዱ የሆነው በቢታንያ አልዓዛር ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም የሚገኘውን ግዙፍና ዘመናዊ የአረጋውያን መጦሪያና ማረፊያ ቅዱስ ሥፍራ ጎብኝተዋል፡፡
ይህ ሥፍራም በቀደማዊው ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ እና በብፁዕ አቡነ አቡነ አብሳዲ፣ አባ ገብረ ማርያም የገዳሙ መጋቢ በነበሩት ዘመን ከንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ገንዘብ ጠይቀው ለሥርዐተ ቀብር ማስፈጸሚያ የሚሆን ቦታ ገንዘብ ተቀብለው የገዙት እንደሆነ ይነገራል።
ከዛን ጊዜ ጀምሮ ቤተክርስቲያኒቱ ስትገለገልበት ከቆየች በኋላ አሁን ያለው ግዙፍና ዘመናዊ ሕንጻ ደግሞ ለአረጋውያኑ መጦሪያና ማረፊያ እንዲሆን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መለካም ፈቃድ በወቅቱ በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ በነበሩት በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ጥረትና ክትትል የተሠራ መሆኑን የገዳሙ የታሪክ መዝግብት ያስረዳሉ፡፡
የአረጋውያኑ መጦርያ ለብዙ ዘመናት በሀገረ ኢየሩሳሌም በተለያየ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ስያገለግሉ የነበሩ እና በሀገረ እስራኤል የሚገኙ የተለያዩ ይዞታዎች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፍ ሲወጡ ሲወርዱ የነበሩ አባቶችና እናቶች መጦሪያ ሥፍራ መሆኑን ያገኘነው ዘገባ ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም:- በገዳሙ የሚገኘው የኢትዮጵያውያን መካነ መቃብር ዕረፍተ ሥጋ ገትቷቸው በክብር ያረፉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ፣ ብፁዕ አቡነ አብሳዲ፣ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ያረፉበት ቅዱስ ሥፍራ እንደሆነም የታሪክ መዛግብቱ ያስረዳሉ፡፡



