ዓመታዊው የቅዱስ ገብርኤል በዓል ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በተገኙበት በቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ዋለ።
ሐምሌ ፲፱ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ዓ.ም
++++++++++++++++++
ቁልቢ -ምሥራቅ ሐረርጌ
“””””””””””””””””””””””””””””””
ዓመታዊው የቅዱስ ገብርኤል በዓል ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ብፁዕ አቡነ ዱዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተረኛ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት በሙሉና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በቁልቢ ደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ውሏል።
በዋዜማው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ
አሥራ አንድ ሰዓት ድረስ ማኅሌቱ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ልዑካን መካከል ክቡር ሊቀ ሊቃውንት ኃይለሥላሴ ዘማርያም፣ ክቡር ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃና መ/ብ አባ ተክለያሬድ ዘጎርጎርዮስ መ/ር ዶ/ር አካለወልድ ተሰማ መሪነት፣ ከተለያዩ አህጉረ ስብከት በመጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ተቁሞ ያደረ ሲሆን ሥርዓተ ቅዳሴው በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ መሪነት ተከናውኗል።
ታቦተ ሕጉ ከወጣና ዑደት ከተደረገም በኋላ በአውደ ምኅረቱ በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ በዓሉን በተመለከተ ትምህርተ ወንጌል የተሰጠ ሲሆን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንና የገዳሙ ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ያሬዳዊ ዝማሬ አሰምተዋል።
በመጨረሻም በብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ትምህርተ ወንጌል፣ ቃለምዕዳንና፣ ቃለ ቡራኬ ከተሰጠ በኋላ የምሕላ ጸሎት ተደርሶ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።



