የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በጀልባ መገልበጥ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖች አስመልክቶ የተሰማውን ኀዘን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በጀልባ መገልበጥ አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖች አስመልክቶ የተሰማውን ኀዘን ገለጸ።
(#EOTCTV ነሐሴ 1 ቀን 2017 ዓ.ም)
+++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠ የኃዘን መግለጫ፤
“እግዚአብሔር አምላከ ሕያዋን ያነሥአክሙ በትንሣኤሁ
የሕያዋን አምላክ እግዚአብሔር በትንሣኤው ያስነሳችኋል”
(ማቴ 22፡31 ሮሜ6፡5፤ቅዱስ ያሬድ) ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር በአርአያውና በመልኩ የፈጠረው የሰው ልጅ እሾህና አሜከላ ወደምታበቅለው ምድር፣ ጥሮ ግሮ ወጥቶ ወርዶ ወደሚኖርበት ዓለም ከመጣ ጊዜ ጀምሮ መከራ ሥጋን ማስተናገድ መጀመሩ በቅዱሳት መጻሕፍትየተጻፈ፣በተግባርም የምንኖረው እውነታ ነው፡፡
የሰው ልጅ አካለ መኑ አድጎ ራሱን ማወቅ ሲጀምር ሕይወቱን ለማቃናት የተሻለ ነሮ ለመኖር፣ ነግዶ ለማትረፍ፣ ዘርቶ ለማጨድ፣ በሀገሩም ሆነ በሌላው ዓለም ሠርቶ ለማግኘት ብዙ ጥረቶችን ያደርጋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ለተፈጥሮአዊና ለሰው ሠራሽ አደጋ መጋለጡ በሕይወቱ የሚያጋጥመው አሳዛኙ ክስተት ነው፡፡
ጥሮ ግሮ ፣ ወጥቶ ወርዶ ባፈራው ሀብቱ እና ንብረቱ ብቻ ሳይሆን ዳግም የማይተካ ሕይወቱንም ጭምር ለሚያጣው የሰው ልጅ በሕይወተ ነፍሱ ያለው መጽናኛ “የሕያዋን አምላክ እግዚአብሔር በትንሣኤው ያስነሣችኋል” የሚለው ሕያው ቃል ነው፡፡
የምንኖርበት ዓለም በብዙ ሥጋቶችና አደጋዎች የታጠረ በመሆኑ ዘመድ ወገን በሌለበት በባዕድ ምድር ሥጋችን ቢጣልም፣ በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቅን፣ ነፍሳችንም ሕያው ከመሆኗ የተነሣ ጠፍታ የማትቀር መሆኑን ስናስብ እንጽናናለን፡፡ ልንጽናናም ይገባናል፡፡
በቅርቡ ከሀገር ወጥተው በጀልባ ሲጓዙ የነበሩ ወገኖቻችን የጀልባ መገልበጥ አደጋ ደርሶባቸው ሕይወታቸው በማለፉ ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰማው ኃዘን ጥልቅ መሆኑን እየገለጸ፣ በአደጋው ምክንያት ለሞቱት ኢትዮጵውያን ወገኖቻችን እግዚአብሔር ዕረፍተ ነፍስን እንዲሰጣቸው ፣ለቤተስቦቻቸውና ለወዳጆቻቸውም ሁሉ መጽናናቱን እንዲያድላቸው ይጸልያል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በክረምቱ ወራት በሁሉም አቅጣጫ በአንድ በኩል በመሬት መንሸራተትና በድንገተኛ ጎርፍ ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዝናብ እጥረትን በመሰሉ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ ችግር እየገጠማቸው ለሚገኙ ወገኖቻችን ፣ ሁሉም የሰው ልጆች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ
ነሐሴ 1 ቀን 2017 ዓ/ም

