X
የደብራችን የኮተቤ መካነ ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና ቤተ-ክርስቲያን ወልድ ዋሕድ ሰ/ት/ቤት ከደብሩ ከተመሠረተበት ሐምሌ 22 ቀን 1,976 ከወራት በፊት ለደብሩ የሰ/ት/ቤት አገልግሎት እና የደብሩ ምሥረታ ክብረ በዓል አከባበር መንፈሳዊ ዓላማ ባነገቡ ጥቂት ወጣቶች እና አገልጋይ ካህናት ፣ ዲያቆናት አማካኝነት በ1,976 ግንቦት ወር ተመሠረተ።

Contact Info

About

Weld Wahed > About
ስለ ሰንበት ትምህርት ቤቱ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሐገረ ስብከት የኮተቤ መካነ ቅዱሳን ኢያቄም ሐና ቤተክርስቲያን ወልድ ወሕድ ሰንበት ትምህርት ቤት

የደብራችን የኮተቤ መካነ ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና ቤተ-ክርስቲያን ወልድ ዋሕድ ሰንበት ትምህርት ቤት ደብሩ ከተመሠረተበት ሐምሌ 22 ቀን 1,976 ከወራት በፊት ለደብሩ የሰ/ት/ቤት አገልግሎት እና የደብሩ ምሥረታን አስመለክቶ በተሰባሰቡ እና አገልጋይ ካህናት ፣ ዲያቆናት አማካኝነት በ1,976 ግንቦት ወር ተመሠረተ።

ሰንበት ትምህርት ቤታችን ወልድ ዋሕድ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የተመሠረተበትን መንፈሳዊ ዓላማ መሠረት በማድረግ በአካባቢው ለሚገኙ የአጥቢያ ምዕመናን ፣ ለደብሩ ዲያቆናት እና ካህናት የተለያዩ መንፈሳዊ ትምህርቶችን በእለተ እሁድ በማስተማር የጀመረ ሲሆን በዚያን ወቅትም ይሰጡ የነበሩ ትምህርቶችም፡- ትምህርተ ሃይማኖት፤ የቤተክርስቲያን ታሪክ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በተጨማሪም የቅዳሴ ተሰጥኦ እና የመንፈሳዊ ዝማሬ ትምህርት ይገኙባቸዋል፡፡

ትምህርቱ በተመሳሳይ ሁኔታ ሲሰጥ ቆይቶ 1,983 ዓ.ም ላይ ሰንበት ት/ቤቱ የመማር ማስተማር አገልግሎት አቻ ከነበሩ ደብራት ለምሳሌ:- ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰ/ት/ቤት ፣ መንበረ ጸባኦት ቅድስተ ማርያም ቤ/ክ ሰ/ት/ቤት ወ.ዘ.ተ በየሚያስተምሩ መምህራን እንዲመደቡለት በመጠየቅ በክረምት ኮርሱን መስጠት ቀጥሏል፡፡

በሚቀጥሉትም ዓመታት የደብሩ አገልግሎት እየተጠናከረ ሲሄድ የሰ/ት/ቤታችንም የመማር ማስተማር አገልግሎት እንዲሁም የዝማሬ አገልግሎት ላይ በስፋት ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እየተጠናከረ ብሎም ፈር ቀዳጅ በሆኑ አገልግሎቶች ተምሣሌት ሆኗል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤታችን የ41 ዓመት ጉዞ

የኮተቤ መካነ ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና ቤተ-ክርስቲያን ወልድ ዋሕድ ሰንበት ትምህርት ቤት ከምስረታው ጊዜ እስከ ያዝነው 2017 ዓ.ም ድረስ 41 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በእነዚህ የአገልግሎት ጊዜያት በሺህ የሚቆጠሩ አባላትን የልጅነት ፣ የወጣትነት እንዲሁም የጎልማሳነት ጊዜያቸውን ከእግዚአብሔር ቤት ሳይርቁ ፣ ቃለ እግዚአብሔርን እየተማሩ ፣ በዝማሬ እያገለገሉ እንዲኖሩ ማረፊያ ቦታ ሆኖአቸዋል፡፡  

ሰንበት ትምህርት ቤታችን መንፈሳዊነትን ፣ አንድነትን ፣ መደጋገፍን ፣ ክርስቲያናዊ ኃላፊነትን ፣ ጽናትና ምስክርነትን ፣ በፍቅር የተሞላ አገልግሎትን እሴት በማድረግ ለ41 ዓመታት በተለያዩ ሁኔታዎች ሲገለገል ቆይቷል፡፡ 

በሰንበት ትምህርት ቤታችን ውስጥ በርካታ የቤተክርስቲያን ልጆች መሰረታዊ የሃይማኖት ትምህርትን እንዲማሩ ፣ ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለቤተሰብ ብሎም ለሀገር እንዲጠቅሙ ፣ በስነ-ምግባር የታነፁ ወጣቶች እንዲፈሩ ወልድ ዋሕድ ሰንበት ትምህርት ቤት ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ለዚህም ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት የሰንበት ትምህርት ቤቷን ክብር አስጠብቀው በየጊዜው የሰንበት ትምህርት ቤቱ ሰብሳቢ በመሆን ተሻጋሪ ታሪክን ያስተላለፉ በርካታ በስራ አመራርነት ሲያገለግሉ የነበሩ ወንድሞች እና እህቶች ሚናቸው እጅግ ትልቅ ነው፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤቷ የአገልግሎት ታሪክ ሳይበረዝ እንደውም ከጊዜ ወደ ጊዜ በተሻለ የአገልግሎት ከፍታ እንዲገለገል በማድረግ ለዚህ ደርሰዋል፡፡

በሰንበት ትምህርት ቤታችን ውስጥ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች የሚካሄዱ ሲሆን በዋናነት የትምህርት አገልግሎት ፣ የዝማሬ አገልግሎት ፣ የኪነጥበብ መርሐግብሮች ፣ የገዳማት ጉብኝት እና የንግስ በዓል ጉዞዎች ፣ የንዋያተ ቅድሳት ምርት ፣ የሰርግ እንዲሁም የዝማሬ ካሴት ማጀብ ፣ የተቸገሩ ገዳማት እና አድባራትን መርዳት ፣ የአብነት ትምህርት …….. ወ.ዘ.ተ ይገኙበታል፡፡ በእነዚህም አገልግሎቶች እድሜያቸው 5 ዓመት ከሞላቸው ህፃናት ጀምሮ በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ሁሉም በተሰማራበት የአገልግሎት መስክ እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲያገለግል ዘወትር ክትትል እና ድጋፍ ለሁሉም አባላት ሲደረግ ቆይቷል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤታችን አሁናዊ አገልግሎት

ሰንበት ትምህርት ቤታችን ለረጅም ዓመታት በብዙ አገልግሎት የተቃኘ ሲሆን እነዚህን አገልግሎቶች ከመቼውም ጊዜ በይበልጥ በአሁን ሰዓት የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት በተለይም ሰፊውን ምዕመን ታሰቢ ያደረጉ የትምህርት መርሃ ግብሮችን በመዘርጋት ቃለ እግዚአብሔርን በስፋት ለማዳረስ ዘርፈ ብዙ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ማለትም (አዲስ አበባም ከአዲስ አበባም ውጪ) የሚገኙ ምዕመናን ፣ የአጥቢያው ምዕመናን ፣ ሰንበት ተማሪዎችን ፣ የአካባቢውን ታዳጊ ወጣቶችን ያማከለ በተለያየ መልኩ የትምህርት መርሃ ግብር በመቅረፅ ቃለ እግዚአብሔር እንዲታላለፍ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ይደረጋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪም በሰንበት ትምህርት ቤታችን በቋሚነት ነዳያንን የማስተማር ፣ የመመገብ እንዲሁም የተለያዩ ቁሳቁሶችን ድጋፍ የሚደረግበት መርሃ ግብር ሲኖር በዚህ መርሃግብር ነዳያንን በቁሳቁስ ከመደገፍ በተጨማሪ ቃለ እግዚአብሔርን እንዲማሩ እንዲያውቁ ከፍተኛ ስራ ይሰራል፡፡ በተጨማሪም አጥቢያው ምዕመናን የሚያሳትፍ የንግስ ክብረ በዓል ጉዞ እንዲሁም የገዳማ ጉብኝት ጉዞ በተለያዩ ጊዜያቶች እየተዘጋጁ ምዕመናን በረከት እንዲያገኙ ከፍተኛ ስራ ይሰራል፡፡

ጋብቻቸውን በቤተክርስቲያን የሚያደርጉ ምዕመናን የሰርጋቸው ዕለት በዝማሬ በልዩ መልኩ በማጀብ በቤተክርስቲያን የሚደረጉ ሰርጎች በአጠቃላይ ውብ እና አስደሳች እንደሆኑ እና ብዙ ምዕመናን ሰርጋቸውን በቤተክርስቲያን ለማድረግ እንዲነሳሱ ትልቅ አስተዋፅኦ በሰንበት ትምህርት ቤታችን ይደረጋል፡፡ እንዲሁም የዝማሬ ቪዲዮ ቀረፃ ላይ ከዘማሪያን ጋር አብሮ በመሆን አገልግሎት ይከወናል፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤታችን ከህፃናት ጀምሮ እስከ ጉልምስና እድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ቁጥራቸው ከሺህ የሚበልጡ አባላትን በውስጡ በመያዝ አመቱን ሙሉ በደብሩ የሚከበሩ በዓላትን እንዲሁም ሌሎች ደብራት ላይ በመሄድ በደብሩ የሚከበሩ የንግስ በዓላትን በጋራ በመሆን የማገልግል እና ቤተክርስቲያን በምትፈልገው ስራ በአጠቃላይ የመሳተፍ ዘገልግሎት በስፋት ይከወናል፡፡

ሰንበት ትምህርት ቤታችን ላለፉት 41 ዓመታት በደብራችን ቅጽር በሚገኙ ሁለት ቦታዎች ላይ ማረፊያውን አድርጎ ሰፊ የሆነ አገልግሎት ሲሰጥበት ቆይቷል፡፡ ይሁንና የሰንበት ትምህርት ቤቱ አገልግሎት ዘርፈ ብዙ በመሆኑ እና ከፍተኛ የሆነ የአባል ብዛት በመኖሩ በአዳራሽ ጥበት ብዙ እንግልት አሳልፈናል፡፡ ይሁን እና ሰንበት ትምህርት ቤታችን አዲስ ሁለገብ የሆነ ሕንፃ ግንባታ ለመጀመር እና የአገልግሎት አድማሳችንን ለማስፋት የካቲት 11/2016 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የተዋሕዶ ሚዲያ የበላይ ጠባቂ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በሆኑት በብፁዕ አቡነ ሄኖክ አማካኝነት የሠሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡

እንደ እግዚአብሔር አምላክ መልካም ፈቃድ በዚህ ሁሉ ዓመታት በሰንበት ትምህርት ቤታችን ሲገለገሉ የነበሩ አገልግሎቶችን በቀጣይ በይበልጥ ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም ጊዜውን እና ዘመኑን የዋጁ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ለመስራት ታስቧል፡፡ “በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” የሚለውን የአምላክ ትእዛዝ በመከተል ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ወጣት በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ አካታች በሆነ አገልግሎት ውስጥ እንዲሳተፍ እንዲሁም ብዙ የትምህርት መርሃ ግብሮችን የማዘጋጀት እቅዶች ተይዘዋል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ተጠብቆ ሳይለወጥ ሳይበረዝ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ የማድረግ እንዲሁም ማንኛውም የቤተክርስቲያኒቱ ተከታይ የሆነ ምእመን የሃይማኖቱን ሥርዓት በውል እንዲያውቅና እንዲረዳ ለማድረግ ሰፊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ይገኛሉ ::

 

በዋናነት በአሁኑ ሰዓት በሰንበት ትምህርት ቤታችን በርካታ አገልግሎቶች ቢኖሩም በቂ የሆነ አዳራሽ አለመኖሩ በተፈለገው ልክ ለመንቀሳቀስ አልተቻለም፡፡ ስለሆነም የሰንበት ትምህርት ቤታችንን ሁለገብ ህንፃ ለማስጀመር እና ለመስራት ሁሉም እኩል ተሳትፎ የሚያደርግበት ትልቅ እቅድ ተይዞ እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡

.